ስምን ክህሎት ያወጣዋል

በ21ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በአንዱ አርብ ቀን ወደ ሀገር ፍቅር ጎራ ብዬ፣ በወቅቱ በብዛት ሲታይ ከነበረ የመድረክ ቲያትር ውስጥ ጎልቶ የወጣ አንድ ወጣት ተዋናይን ቲያትሩ ካለቀ በኋላ ተዋውቄ ለትንሽ ጊዜ አውግተን ተለያየን።

ከወራት በኋላ ይሄው ወጣት፣ በደራሲነት፣ በአዘጋጅ እና በተዋናይነት የተሳተፈበትና የከተማው መነጋገርያ እየሆነ የመጣውን ድራማ ከታደምኩኝ በኋላ ከፒያሳ ዑራኤል ድረስ ከአንድ ወዳጁ ጋር አብረን “ዎክ” አደረግን። ስለ ብዙ ነገር ተወያየን። ድራማው “ሳታየር” ለሚባለው ዘውግ የተጠጋ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን እያዋዛ የሚከት ስለነበር፣ ቢካተቱ ይጠቅማሉ ያልኳቸውን ነጥቦች ነግሬው ባምቢስ ጋር ተለያየን።

ከወራት በኋላ የ”ውጭ” እንግዶችን ይዤ ድራማውን ልመለከት ስሄድ ይዘቱን ሳይቀይር ብዙ ወቅታዊ የሆኑ ነገሮችን ( እኔ ያቀርብኳቸውን ሶስቱን ጨምሮ)  በግምት 30%ቱ ተቀይሮ ጠበቀኝ።

ይህ ተዋናይ ይህን ድራማ ለዓመታት እያሻሻለ መስራቱን ቀጥሎ፣ በመሀል ብዙ ፊልሞችን መስራት ጀምሮ ወቅቱ በፈቀደው ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በየሲኒማ ቤቱ ቋሚ አቅራቢ ሆነ።

ከዚያ የፒያሳ ዑራዔል ጉዞ በኋላ ጥቂት ቦታዎች ብንተያይም፣ ለዓመታት በቴሌቪዥን አየዋለሁ እንጂ በአካል ተገናኝተን አናውቅም።

ከጥቂት ወራት በፊት አንድ ምግብ ቤት አገኘሁት እና ትንሽ አወጋን። ወደ አሜሪካ ወጣ ብሎ ለትንሽ ዓመታት ቆይቶ ከተመለሰ በኋላ የሁለት ሀገር ሰው ሆኖ የተለያዩ ነገሮችን እየሞከረ መሆኑን እና ያ የተወደደለትን ቲያትር በአዲስ መልክ እንደጀመረው ነገረኝ። እኔም ለመጨረሻ ጊዜ ካየሁት በትንሹ 10 ዓመት  ስላለፈ፣ ቢያንስ ለውጡን ልመልከት ብዬ፣ የዛሬ ሁለት ወር ከስራ ባልደረባዎቼ ጋር ቲያትሩ ወደሚታይበት ቦታ አቀናሁ።

“በዳዊት እንዚራ ” ለመጀመርያ ጊዜ ያየሁት እና በ”ፍሬሽ ማን ” የተዋወቅሁት ነፃነት ወርቅነህ፣ በጎልማሳነቱ ዘመን እንደ ወጣት እየተጫወተ፣ ቅርፁ ያው ቢሆንም  ይዘቱ ግን ጊዜውን የዋጀ አድርጎ “ፍሬሽ ማን “ን በአዲስ መልክ አቅርቦልን ተመለከትኩ።

ስምን መልዓክ ያወጣዋል ቢባልም ስምን ክህሎት ያወጣዋልም ባይ ነኝ። ነፃነት፣ በነፃነት የሚያስብ መሆኑን በሚገርም ብቃት አሳየን። ትላንት፣ በሳምንታት ውስጥ፣ ለሁለተኛ ጊዜ  ለማየት ከጓደኞቼ እና ወዳጆቼ  ጋር በዛ ብለን ልመለከተው ሄደን አየነው፤ ሳላጋንን 20 በመቶው ተቀይሮ ይበልጥ ” ወቅታዊ ” ሆኖ ጠበቀኝ።

ነፃነት በተፈጥሮ የተለገሰው ልዩ የሆነ የማሳቅ ችሎታ አለው። በጣም ፈጣን “ፕሮሴሰር ”  አዕምሮ እና አጅግ በጣም ጥሩ የሆነ “ኦብዘርቭ” የማድረግ ችሎታ አለው።

ለማንም ሳይመለስ፣ በጣም መደበኛ የሚመስሉ፣ ግን በሳቅ የተለወሱ ከባድ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እና  የትውልድ ጉዳዮችን በሚገርም ትስስር እና ቅንጅት እያሳቀ ” ሶሻል ክሪቲኩን ” አቅርቦአል።

“ኮሜዲ” ፈታኝ የሆነ ስራ ነው ። ፅሞናን ፣ ማስተዋልን ፣” ታይሚንግን” ፣ የቋንቋ ችሎታን ጨምሮ ተሰጥዖን ይጠይቃል። ነፃነት፣ እነዚህን ሁሉ አጣምሮ የያዘ ድንቅ የመድረክ ሰው ሆኖ ተገኝቷል፡፡

Ebs በተባለው ቴሌቪዥን፣  የቤተሰብ ጨዋታ የተሰኘውን የቤተሰብ የጥያቄና መልስ ፕሮግራም፣ ተወዳጅ ያደረገው ነፃነት በዝግጅቱ ላይ የሚሰጣቸው ቅፅበታዊ እና አሁናዊ መልሶቹ አዝናኝ ብቻ ሳይሆኑ ከአውዱ እና ከተጠያቂዎቹ ጋር ልክክ የሚሉ ናቸው።

በእኔ እይታ፣ የነፃነት የአማርኛ ቋንቋ ችሎታ ልዩ ነው። የቃላት ጨዋታዎቹ ከቋንቋ ክህሎቱ እና ከሚያውቀው ጥልቅ ትውፊት ጋር ተጣምረው በተፈጥሮ ከተቸረው የማሳቅ ችሎታ ጋር ተደምሮ በእኔ አረዳድ፣ በአሁኑ ወቅት በሀገራን አሉ ከሚባሉት “ኮሜዲያን ” ተርታ አሰልፈዋለሁ።

አንዳንድ ሰዎች “ስታይሉ” አንድ ዓይነት ነው ብለው ቢተቹትም  በኮሜዲው ዓለም፣ ሚስተር ቢን፣ ጂም ኬሪ ፣ ኬቨን ሃርት አና ክሪስ ሮክን የመሳሰሉ ዓለም ዓቀፍ ኮሜዲያንም ተመሳሳይ “ስታይል” ይዘው ዓለማቀፋዊ ስለሆኑ፣ ይሄንን ትችት ብዙ አልቀበለውም።

አሁን አሁን እየቀነሰ ቢመጣም ከመጠን በላይ ፈጥኖ የሚያወራው ( አንዳንድ ጊዜ ለአድማጭ በሚያስቸግር ሁኔታ) ነገር፣ በፊልሞቹ ላይ የሚስተዋለው የድምፅ እና ምስል ጥራት ችግር፣ በድሃ እና ሃብታም ላይ በብዛት ያተኮሩ ድርሰቶች እና አብዛኛው ስራዎቹ በእርሱ ዙርያ ማጠንጠናቸው እኔም የምስማማባቸው ምክንያታዊ ትችቶች ናቸው።

ጥልቅ በሆነ ዕይታ ባለፉት 5 ዓመታት ውስጥ እነማን  ያስቁሃል ብባል በአዳዲስ ኮንቴንት  ኮሜዲያን (“ፓስተር”)  ቶማስ ፣ በፖለቲካ እና ማህበራዊ ፅሁፎቹ አንዱአለም በዕውቀቱ እና ቃላት የሚጎርፉለት ነፃነት ወርቅነህ ናቸው።

ለየት ያለ “ስክሪፕት ” ፣ አዘጋጅ እና በጀት ያለው ከኮሜዲ የወጣ ፊልም ወይም ድራማ ላይ ቢሳተፍ  ነፃነት ሌሎች ገፀ- ባህርያትን ልዩ አድርጎ እንደሚተውን እርግጠኛ ነኝ። ያሳየናልም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

በፊቱም የሚተውነው ነፃነት ለእራሱም የማይመለስ በራሱ የሚቀልድ እና ሪድክ ወሳጅ ከተሜ ነው። በቤተሰብ ጨዋታም ሆነ በፍሬሽ ማን ላይ በጣም ከባድ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮችን በሳቅ እያዋዛ ያቀርባል። ማህበረሰብም መንግስትም ከእንደዚህ አይነት ባለሙያዎች በብዛት ይጠቀማል ብዬ አምናለሁ፤ ለዛውም ብዙ የጥናት ወጪ ሳወጡ።

ድሮ ድሮ፣ “እረኛ ምን አለ?” ይባል ነበር ። የዘንድሮ ነቃሾች እንደ ነፃነት አይነት እውነት ነጋሪዎች ናቸው ” ምን አሉ? ” መባል ያለባቸው።

ከተለመዱት አሰልቺ ቃለ-መጠይቆች አልፎ፣ ሙያው እና ማንነቱ ላይ ያተኮረ መድረክ ቢያገኝ ፍልስፍናውን እና ልምዱን የሚያካፍልበት ” ፕላትፎርም ” ይሆናል ብዬ አስባለሁ ። ማን ያውቃል ደጃፍ ላይ ብቅ ይል ይሆናል። የራሱንም ሊያበጅ ይችላል ።

ከድራማው ላይ ቢሻሻሉ እና ቢቀነሱ የምላቸውን  ትንሽ የሚጎረብጡ ነገሮችን በፅሁፍ አቀርብልሃለሁ ። በተረፈ ግን በርታ!

ነፃነት ይመችህ የኡራዔል ልጅ!  እውነትም ስምን ክህሎት ያወጣዋል፣ የአንተ ደግሞ ከነአባት ነው! 

ነፃነት እውነትም ወርቅ ነህ! 

ማገቦ

ነሃሴ 2014

*ፍሬሽ ማን አለም ሲኒማ ዘወትር እሮብ እና አርብ ከምሽቱ 12: 30 ጀምሮ ይታያል። ጎራ በሉና እዩት፤ አልወደድኩትም የሚል ካል የትኬቱን 3 እጥፍ ተመላሽ አደርጋለሁ።
ማገቦ
Author: ማገቦ


Dahabesha

Our mission is to inspire, empower and connect Habesha people around the world by providing accurate, up-to-date news and information about the culture.