የሃገር ቤት ጉዞ

እሁድ ጠዋት  12:55 ሰዓትመነሻውን ከግዮን ያደረገው የ BCAA ቤተሰብ ስብስብ የነቃው ያልነቃውን እያበረታ በገላን አድርጎ በኃይሌ ጋርመንት በሀጫሉ ሁንዴሳ አስፓልት በኩል በተፍኪ፣ ተጂ አቋርጦ አምስት ሰዓት ላይ የቁርስ እረፍት ካደረገ በኋላ በወሊሶ እና ወልቂጤ በኩል መዳረሻው ወደሆነው አገና ወረዳ፣ ቅጣነ ቀበሌ በ9:12 ሰዓት ደርሰናል።

እንደደረስንም ማረፊያችንን አስተካክለን የተዘጋጀልንን የመጀመሪያ የበዓል መአድ የጎመን ክትፎ በአይብ ተመግበናል። ጣዕሙን ለማስረዳት መሞከር አንባቢን/ተመልካችን ማድከም ነው።

በቀጣይም ትንሽ እረፍት ካደረግን በኋላ በባህሉ ደንብ መሠረት በቤቱ ታላላቅ ሰዎች ከተመረቅን በኋላ እርድ ሲከናወን ተመልክተናል። አንዳንድ ከበሬው ጋር ያላቸው የጠብ ዝምድና ያልተጣራ የቤተሰባችን አባሎችም በጠልፎ መጣሉ እና በመያዙ ሂደት ከፍተኛ ተሳትፎ አሳይተዋል። የፈራን ዳር ሆነን ሂደቱን ብንቀርጽም ለእናንተ ለማጋራት የፖሊሲ ክልከላ ስላለብን ባወራን እመኑ ብለን እናልፋለን። ከዛማ ምኑ ቅጡ ተጫውተን፣ ሞያ አለን ያልን ከማጀት ገብተን፣ ሌሎች እሳት በማቀጣጠል ተሳትፈው እራታችንን ከዝናብ ለማስጣል ከባድ ግብግብ አካሂደን በረንዳው ላይ እየሳቅን እና እየተጫወትን የማረፍያ ልብሶቻችንን ከቀየርን በኋላ ያላለቁ ጨዋታዎቻችን ደርተው የኳየሩም የካበተ ልምድ ታክሎበት ምሽታችን አድምቀን ዘግተናል።

ሰኞ ማልደን “ደርሳችኋል ቅርብ ናት” የተባለች የአራት ኪሎ ሜትር እግር መንገድ አገባደን ከከፍታው አናት ላይ ባለችው ያስያ ምድረሊባኖስ ቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን ተገኝተናል። ካህኑ ጸሎቱን ካሳረጉ በኋላ በአራቱም አቅጫጫ ተዟዙረው የለኮሱትን ደመራ በእልልታ አጅበን፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ተጨዋውተን እና ፎቶ ተነስተን “ዓመት ዓመት ያድርሰን!” ተባብለን ዳግታ ያስቸገረችንን መንገድ ወርደን ወደ ቤታችን ተመልሰን ቁርስ ካደረስን በኋላ ግማሹ ሰፈር ለማየት፣ ገሚሱ ደግሞ በመኝታ አዳባዩ ማንኮራፋት ያልጨረሰውን እንቅልፍ ሊቋጭ በየፊናችን ሆንን። ከተማ ሄደን ሥራ እንድንከውን የተላክንም ከተማ ሄደን ቡን ቀመስን አንዳንዶችም አሉ የእዣን የሰኞ ገበያ ለመቃኘት የቻሉ። የታዘብነው ነገር እምብዛም የማሽን ቡና እና ሻይ ያልተለመደ መሆኑን ነው።

ስንመለስ ሰፈር አሳሾቹ የፏፏቴ ግኝት ማካሄዳቸውን፣ የተኙት ጥሩ ህልም ማየታቸውን እንዲሁም ለሥራ የተላክነውም መከወናችንን ራፖር ከተቀያየርን ወዲያ የክትፎውስ ነገር ለምትሉን ያው ተበላ! ተጠጣ! እንላችኋለን።

ፀሐይ አዘቅዝቃለች፤ የሰፈራችን ልጆች እየተጣሩ ነው። የሰፈራችንን ዳመራ ልናበራ በሀገርባህል ልብሶቻችን አሸብርቀን ከቤተሰቦቻችን ጋር ለምርቃቱ አሜን! ብለን ለጨዋታው አለን ብለን አጨብጭበን፤ ለፎቶዎቻችንም ፈገግ ሸብረቅ ብለን ደመራን አክብረናል። አላሳፈርናችሁም። እንዴት ነው እራት በላችሁ? እኛ በልተን የደመራ ማጥፊያው ዝናብ ያስከተለውን ብርድ ለመከላከል ጎርደቱን ከበን እየተጫወትን ራሳችንን ለማሞቅ አባባ ያስነደዱልንን እሳት እየሞቅን ነው። ነገ ተመላሽ ተጓዦች ነን፤ በሉ እማማ እንዳሉ ‘ተኙ!’

ሰኞ ሁሉ ሲለዩት ባር ባር ይላል። ከማረፊያችን ይዘን የመጣቸውን እቃዎች እንዳንዘነጋ ሸክፈን መኪናችንን ላይ ጭነናል። ግማሾቹ አሳሾቹ አገኘን ያሉትን ፏፏቴ ሳንዝናናበት ያሉ እነሱን ተከትለው ሲሄዱ ቤት የቀረን እትዬ ወርቅነሽ እና እየሩስ ያዘጋጁንን ቁርስ እየተመገብን እነሱን መጠበቅ መረጥን። እንደ ጨው ነጭ እስኪሆኑ ተንቦራጭቀው ከመጡ በኋላ እነርሱም ቁርሳቸውን ከበሉ ወዲያ ያስተናገዱንን ሁሉ ካመሰገንን በኋላ በ6:45 ከአገና ተነስተን ሙዚቃ እያደመጥን በጉበሬ፣ ወልቂጤ አልፈን ወሊሶ ስንደርስ ከኔትወርክ ተቆራርስጠን የከረምንባቸውን ዜናዎች ስናስስ የሕልፈት ዜና አንብበን አዝነናል። መጽናናትንም ለሁሉ እንመኛለን።

ከወሊሶ የቡና እረፍት በኋላ በዲለላ፣ከታ፣ ተጂ አልፈን በተነሳንበት ቅደም ተከተል እየተመለስን ነው።

በየመዳረሻዎቻችን ለተቀበላችሁን፣ ቤታችሁን ከፍታችሁ ላስተናገዳችሁን ሁሉ ምስጋናችን ከልብ ነው።

Martha, a ምጥን ሽሮ ተመጋቢ, enjoys reading books and she is a member of multiple book clubs on Club House. You can find her podcast, Martha’s Point on Spotify . You can also follow Martha on the following social media platforms.All photos are taken and owned by Martha.
Twitter: @Marthas_point  Instagram: @marthas_point30  Club House: @marthaspoint
Dahabesha
Author: Dahabesha

@dahabesha


Dahabesha

@dahabesha

Dahabesha

Our mission is to inspire, empower and connect Habesha people around the world by providing accurate, up-to-date news and information about the culture.